Saturday 28 January 2017

የምንታገለው ስልጣን የህዝብ ሀብት መዝረፊያ መሳሪያ መሆኑ እንዲቆም ነው!!! አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ


ምርጫና የፖለቲካ መሪ ለውጦች በአለማችን ብዙ ሀገሮች በተለይ በዳበሩት ሀገሮች ካለምንም ውጣ ውረድ የሚከናወኑ የመንግስት ስርዓት መናጋት የማያስከትሉ በየጥቂት አመታቱ የሚከወኑ ክስተቶች ናቸው።
በነዚህ ሀገሮች ስልጣን የጥቅም መሰብሰቢያ መሳሪያ አይደለም። በነዚህ ሀገሮች ባለስልጣኖችና የህዝብ ተመራጮች ጥቅም ካገኙም የሚያገኙት ከስልጣን ከለቀቁ በሁዋላ ነው።
በአሜሪካ እንደ ፕሬዚዳንት ክሊንተን አይነት ከቤተ መንግስት ሲለቅ ትርፍ ሳይሆን ዕዳ ይዞ የወጣ ፕሬዚዳንት አለ። አሁን የብዙ ሚሊዮን ባለሀብት ቢሆኑም ሀብታቸውን ያፈሩት ከስልጣን ከወረዱ በሁዋላ ነው። ያሁኑ ተመራጭ ዶናልድ ትረምፕ በህዝብ ምርጫ የያዙት የመንግሥት ስልጣን ከግል የንግድ ኩባንያቸው ጥቅም ጋር እንዳይጋጭ የሚያደርጉበትን መንገድ እንዲያበጁ ወዳጅም ጣላትም አየወተወተ ይገኛል።
ይህ እየሆነ ያለው ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ወይም በስልጣናቸው ምክንያት ጥቅም እንዳያገኙ ተብሎ ነው። የጥቅም ግጭት (Conflict of interest) ይሉታል። የመንግስት ሹመት የሹም መገልገያ እንዳይሆን የሚደረገው ቁጥጥር በሠለጠኑ አገሮች የተለመደና የህዝቡ ባህል አካል ከሆነ ቆይቶአል።
ዛሬ አለማችን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ስልጣን መዝረፊያና መክበሪያ እየሆነ ያለው በአብዛኛው እንደኛ ኢትዮጵያ ባሉ ኋላ ቀር ሀገሮችና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ብቻ ነው።
ከአገራቸውና ከህዝባቸው ጥቅም በላይ የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ ሲሉ በተለያየ መንገድ የመንግሥት ሥልጣን ተቆጣጥረው ያሉ እነዚህ የአገራችንና የሌሎች አፍሪካ አገሮች መሪዎች እጅግ በሚያሳዝን እና ሀፍረተቢስ በሆነ ሁኔታ ከፍተኛ የህዝብ ሀብት ዝርፊያ ተግባር ላይ በመሠማራት በሚሊዮን የሚቆጠረውን ወገናቸውን ለከፋ ድህነት ይዳርጉታል።
በተለይ በአገራችን በፊውዳሉ ዘመን የነበረው “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የዘራፊዎች መፈክር ከምንጊዜውም በከፋ ሁኔታ በወያኔ ዘራፊዎች እየተገበረ ነው።
በቅርቡ በጋምቢያ ምርጫ ተካሂዶ በውድድር የተሸነፈው ፕሬዚዳንት መሸነፉን ከተቀበለ በኋላ ስልጣኑንና ጥቅሙን ላለማጣት ሰበብ ፈጥሮ በጉልበት ለወራት ከቆየ በኋላ የጎረቤት ሀገሮች የማይለቅ ከሆነ በተባበረ ጦር ወግተው ለማስለቀቅ ውሳኔ እንዲያሳልፉ አስገድዷቸዋል። ይህንንም በመፍራት በሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ሀብትና ውድ መኪናዎች ባውሮፕላን ጭኖ ከሀገር ለመልቀቅ ወስኗል። ይህ ግለሰብ በድርጊቱ እንዳች ሀፍረት የተሰማው አይመስልም። ዝርፊያውን እንደገድል ሳያየው የቀረም አይመስልም።
እነዚህ ዘራፊ ባለስልጣኖች በዚህ አይናውጣ የሌብነት ስራ የሚሰማሩት ስልጣናቸውን ለህዝብ ውሳኔ አሳልፎ መስጠትን ከህሊናቸው አውጥተው ስለጣሉ ነው። ለዚህም ነው ህዝብ ጥያቄ ይዞ በተነሳ ቁጥር ካለርሕራሄ የሚጨፈጭፉት።
ለዚህ ነው ስልጣናቸው ዘላለማዊ እንዲሆን ሌት ከቀን የሚሟሟቱት። ስልጣናቸውን ያጡ ቀን የሚያጡት ስልጣን የሰጣቸውን የዝርፊያ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ዘርፈው ያጠራቀሙትን ሁሉ እንደሆነ ያውቃሉ።በዚህም የተነሳ የህዝብ ዳኝነት ይፈራሉ በሚገዙት ሀገር ፍትህ ኖረ አልኖራ ደንታ የላቸውም። ብቻ ሳይሆን ነገ በነሱ ላይ የሚበየነው ፍርድ እየታያቸው በተከበረው የፍርድ ስራ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ፍትህ እንዲዛባ ያደርጋሉ።
የኛ አገር ወያኔዎች ከእንደዚህ አይነቶቹ ሌቦች ተርታ ናቸው። ስልጣናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግና በህግና በሰላም ሳይቀር የሚቃወሙዋቸውን ካለርህራሄ ወህኒ የሚያጉሩትና የሚገሉትም ለዚህ ነው።
ለዚህ ሁሉ የባልስልጣኖች ዝርፊያና ዕብሪት በሹማምንቱ ላይ ስናማርር በተወሰነ ደረጃ ካለገደብ ለሚደርስብን ዝርፊያ ራሳችንም እንደህዝብ ተጠያቂዎች ነን።
ስልጣንን መዝረፊያ እንዳይሆን ያደረጉ ሀገሮች ህዝቦች ይህን የተቀዳጁት ቁጭ ብለው በመመልከት ወይም ተቀምጠው በሹክሹክታ በማማረር አይደለም። መስዋዕትነት ከፍለው ታግለው ነው። በየሀገራቸው ህግ ከሰው ሁሉ በላይ የሆነበት ስርዓት ስለመሰረቱና ይህም እንዳይፈርስ ነቅተው ስለሚጠብቁ ነው።
በስማቸው እየማሉ የሚያጭበረብሩ ምሪዎችና የህዝብ ተመራጮች መብታቸውንም ሀብታቸውንም እንዳይዘርፉ አጥብቀው ባርበኝነት ስሜት ስለሚጠብቁ ነው። ባጭሩ ህዝብና ህግ የሚፈሩ እንዲሆኑ የሚያደርግ ስርዓት ስለመሰረቱ ነው።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የትግል ግብ እንዱና ምናልባትም ዋነኛው ይህን የዝርፊያ አዙሪት አጥፍቶ ህዝብና ህግ የበላይ የሆነበት ስርዓት መፍጠር ነው።
ህዝባችንን ነጋ ጠባ ለትግል የምንጠራው ከዚህ አይነት የውርደት ህይወት እንድንወጣና በህግ ስር የምትኖር ሀገር እንድትኖረን ነው። ከዚህ ውጭ ጥቂቶች እየተንደላቀቁ በሚኖሩበት ሀገር ብዙሀኑ ህዝብ በዘግናኝ ድህነት ሰር የስቃይ ኑሮውን መግፋት ብቻ ነው አማራጩ። ይህ እንዲሆን የማትፈቅድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቢያንስ በያለህበት ሆነህ ተቀላቀለን።
ወያኔን የመጨረሻው የሀገራችን ዘራፊ መንግስት ለማድረግ የተያያዝነውን ትግል በተባበረ ሀይል በፍጥነት ዳር እናድርስ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!