Sunday 11 June 2017

የሰኔ-አንድ-ሰማዕታት-አደራ-በትግላችን

ሰኔ አንድ በኢትዮጵያ የሰማዕታት ታሪክ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓም እንደ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓም ሁሉ ፣ መብታቸውን የጠየቁ፣ በባርነት፣ በጭቆና እና በዘር መድሎ አንኖርም ያሉ ኢትዮጵያውያን በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ደማቸው እንደ ጎርፍ እንዲፈስ የተደረገበት ዕለት ነው። በየካቲት 12 እና በሰኔ 1 መካከል ልዩነት ቢኖር፣ የገዳዮች ማንነት ነው። የካቲት 12 ቀን 2009 ዓም የአገራቸውን በጣሊያን መወረር የተቃወሙ የቁርጥ ቀን ልጆች በፈጸሙት ታሪካዊ የአልገዛም ባይነት ተጋድሎ ፣ በአረመኔው ግራዚያኒ ትእዛዝ ተጨፍጭፈዋል። ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓም ደግሞ የጭቆናን ቀንበር ሰብረው ለመውጣት ትግል ያደረጉ፣ በአገራቸው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተገንብቶ ማየት የሚሹ፣ በግንቦት 7 1997 ዓም ምርጫ ወላጆቻቸው የሰጡት ድምጽ እንዲከበርላቸው የጠየቁ እንቦቀቅላዎች፣ አገር በቀል በሆነው የግራዚያኒ የመንፈስ ልጅ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ፣ ከ40 በላይ ወጣቶች በአደባባይ የተጨፈጨፉበት፣ ብዙዎች ለአካል ጉዳትና ለእስር የተዳረጉበት ነው።
እነዚህ ሰማዕታት የህይወትና የአካል መስዋትነት ሲከፍሉ በህይወት ላለነው ታላቅ አደራ አስቀምጠውልን ማለፋቸውን ምንጊዜውም ልብ ልንል ይገባል። ሰማዕታቱ “ኢትዮጵያችን ዘረኝነትን፣ ጭቆናንና አፈናን አሸንፋ፣ በዲሞክራሲ፣ በፍትህና በነጻነት የምትመራ አገር እስከምትሆን ድረስ ትግላችሁን ቀጥሎ፣ ያን ጊዜ የእኛ ደም ከንቱ ሆኖ አየቀርም” የሚል አደራ አስቀምጠውልን አልፈዋል። ይህ ታሪካዊ አደራ ዛሬ ዛሬ እየተደረገ ላለው የሞት ሸረት ትግል የማንቂያ ደወል ሆኖ እያገለገለ ነው። ዛሬ በመላ አገራችን የተቀጣጠለ የመጣው የነጻነት ትግል ለእነዚህ ሰማዕታት ትልቅ ርካታን የሚሰጥ ነው። በእያንዳንዱ ቀን በምናደረገው ትግል ውስጥ ሰማዕታቱ አብረው ይዘከራሉ።
የሰኔ 1 ሰማዕታትን አደራ ጠብቀው የተጓዙ በርካታ ወጣቶች የህይወት መስዋትነት ከፍለዋል፣ እየከፈሉም ይገኛሉ። ከሰኔ 1 ቀን 1997 ዓም ወዲህ በማላ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለነጻነታቸው የህይወት መስዋትነት ከፍለው። በአወዳይ፣ አምቦ፣ ሃሮማያ፣ አርሲ፣ ጎንደር፣ ጎጃም እና በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄዱ የነጻነት ትግሎች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ2 ሺ ያላነሱ ሰዎች በአረመኔው አገዛዝ በግፍ ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በየእስር ቤቱ እየማቀቁ የሚገኙትንማ ቤት ይቁጠረው። የሰኔ ሰማዕታት የለኮሱት ትግል ፣ አደራቸውን በተቀበሉ ወጣቶች እየጎመራ ሲሄድ ስንመለከት ፣ የሰማዕታቱ ደም ከንቱ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ አደራውን በተቀበሉ ወጣቶችም እንድንኮራ አድርጎናል።
ትግል እንደ ዱላ ቅብብሎሽ አንዱ ለሌላው እያስረከበው የሚሄድ ነገር ነው። አንድን ትግል አንድ ግለሰብ ወይም የአንድ ትውልድ አባላት ብቻ ከዳር ያደርሱታል ብሎ ማመን ስህተት ነው። የሰኔ ሰማዓታቱ የትግሉ ሻማ ለዚህ ትውልድ አስረክበዋል፣ ይህ ትውልድ ደግሞ ሻመው እንዳይጠፋ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ እንዲቀጣጠል አድርጎ ለሚመጣው ትውልድ ያስረክባል፣ የሚመጣው ትውልድም ለቀጣዩ ትውልድ እያስረከበ ይሄዳል። የህወሃትን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ ማስወገድ ከትግሉ ግቦች ውስጥ አንዱ ቢሆንም፣ በዚህ አገዛዝ ቦታ ላይ የሚተካውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር ፣ የተፈጠረው ስርዓት በጠንካራ አለት ላይ እንዲቀመጥና ቁመናውንና ጥንካሬውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የትውልዶች ስራ ነው። የዚህ ትውልድ የቤት ስራ የህወሃትን አገዛዝ አስወግዶ በምትኩ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መሰረት መጣል ነው ብሎ ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት7 በጽኑ ያምናል። ለዚህ ስርዓት መመስረትም አስፈላጊውን መስዋትነት እየከፈለ ይገኛል፤ ይህ ስርዓት እውን እስኪሆንም መከፈል ያለበትን መስዋትነት ሁሉ ይከፍላል። አርበኞች ግንቦት7 የሰኔ ሰማዕታት ያስረከቡትን አደራ ምንጊዜም ጠብቆ አደራቸውን ዳር ለማድረስ የሚተጋ ድርጅት ነው። ሰኔ 1 በአርበኞች ግንቦት7 ታጋዮች ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚይዝ ቀን እንደመሆኑ፣ በዚህ ቀን ሁሉም ታጋይ የትግሉን ቃል ኪዳን ያድሳል። ሰማዕታቱንም ይዘክራል።


የሰኔ ሰማዕታት አደራውን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ያስረከቡት በመሆኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ አደራ ዙሪያ ታቅፎ ትግሉን ማካሄድ አለበት። የህወሃትን ዘረኛና ጨፍጫፊ አገዛዝ ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ በተነቀለው ጉቶ ላይ የዲሞክራሲያንና የነጻነትን ችግኝ ለመትከልና ለማሳደግ የመላው ኢትዮጵያዊን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሁላችንም የሰኔ ሰማዕታትን አደራ እያስታወስን እጅ ለእጅ ተያይዘን ትግላችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ዛሬም አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን።
ክብር ለሰኔ አንድ ሰማዕታት! ድል ለኢትዮጵያ ነጻነት ወዳዶች ሁሉ!

No comments:

Post a Comment