Friday 15 May 2015

‹‹ የባለ ስልጣንና የባለ ሀብት ቁርኝት ከየት ወዴት ››


ዛሬ በዓለማችን ላይ ትልቁን ስፍራ ይዘው የሚንቀሳቀሱት አንቀሳቃሽ ሞተሮች ገንዘብና ስልጣን ናቸው፡፡ገንዘብ ለሰው ልጆች በምድር ላይ ሲኖሩ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላትና ለመግዛት አስፈላጊው ነገር ነው፡፡ሀገር በአግባቡ እንድትመራና በሰው ልጆች መካከል መከባበርና ሰላም እንዲኖር ስልጣን ያለው አካል መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ነገር ግን ገንዘብም ሆነ ስልጣንም በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ከጠቃሚነታቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን ይችላል፡፡ማለትም ሰዎች ገንዘብን የሚፈልጉት የሚያስፈልጋቸውን ለመግዛትና ለመኖር እስከ ሆነ ድረስ ምንም ችግር የለውም ነገር ግን በገንዘባቸው ሰውንም ጭምር ለመግዛትና የሰውን መብት ለመንጠቅ የሚጠቀሙበት ከሆነ ግን አደገኛ ነገር ነው፡፡ብዙዎች ገንዘብ የሀይል ምንጭ እንደሆነ በማሰብ በገንዘባቸው ብዙ ሀይል እንዳላቸው ያስባሉ፡፡እንደዚሁም ደግሞ ሰዎች ወይንም ተቋማቶች ስልጣናቸውን መሠረት አድርገው ማህበረሰቡን የሚጠቅም ነገር ሊሰሩበት እንደሚችሉ ሁሉ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ማህበረሰቡን ሊያደቁ ሊያስለቅሱ ሊያስጨንቁ ይችላሉ፡፡ዋናው ነገር ገንዘብም ሆነ ስልጣንም በራሳቸው ክፉ ነገሮች አይደሉም ነገር ግን እንደ አያያዘቸው ነው፡፡ለምሳሌ እሳት በአግባቡ ከያዟት ጠቃሚ ስትሆን ነገር ግን በአግባቡ ካልያዟት ንብረትን አውዳሚ ሰዎችን የምታጠፋ ነገር ናት፡፡ልክ እንደዚህ ገንዘብንና ስልጣንንም ሰዎች በአግባቡ ካልያዙዋት ከጥቅምዋ ጉዳትዋ ያመዝናል፡፡
ዛሬ ሰዎች ስልጣንና ገንዘብን በጣም ይፈልጉአታል፡፡ሁለቱም ተያያዥና ተዛማጅ ነገሮች ናቸው፡፡ገንዘብን መሠረት አድርገው ስልጣንን ይፈልጋሉ፡፡በገንዘባቸው ስልጣንን ወይንም ባለስልጣንን ለመግዛት ይፈልጋሉ፡፡ባለስልጣኑም በስልጣኑ ሀብታሞችን ወይንም ገንዘብ ያላቸውን መግዛት ይፈልጋል፡፡ይህ በሚሆንበት ጊዜ ድሆች ገንዘብ የሌላቸው ገንዘብ ባላቸው ባለ ሀብቶችና ስልጣን ባላቸው ባለስልጣኖች ይረገጣሉ ፍትህ ይጠፋል ፍርዶች ይጣመማሉ ድሆች ያላቸውን ተቀመተው ለባለ ሀብቶችና ለባለስልጣኖች ይሰጣሉ፡፡
ዛሬ በየትኛውም ስፍራ ሰዎች ስልጣን ላይ ለመውጣትና ስልጣንን ለመያዝ የሚሮጡት ለምንድነው ; በእውነት ትልቅ ራዕይና ሸክም ለሰፊው ሕዝብ ኖሮአቸው ይሆንን ; አይመስለኝም፡፡ለምሳሌ እርግጠኛ ሆኜ እንዲህ እንድናገር እያደረገኝ ያለው ነገር ደግሞ ዛሬ በሀገራችን ያሉት ባለስልጣኖች ስልጣን ላይ ያላቸው ሙጭጭ ያለ አቋም ይህንን የሚያመለክት ነው፡፡ለምሳሌ የወያኔ አርነት ድርጅት በ 1983 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ይዞአቸው የገቡት ሰዎች ምን ይመስሉ ነበር ; ትግል ላይ ስለነበሩ ድህነቱ ማጣቱ የተጫወተባቸው ሰዎች መሆናቸውን ማስታወስ አንችላለን፡፡በእርግጥ ነገሮች እንደዚያው ይቀጥሉ ለምን ተለወጡ ማለቴ አይደለም፡፡ነገር ግን ሕልማቸው ሞልቶ ዓላማቸው ሲሳካ ግን ስለ ድሆችና ስለ ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልታገሉ መሆናቸውን በድፍረት አፋችንን ሞልተን እንድንናገር ያስችለናል፡፡አንዳንዶቹ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በ20 ዓመታት ውስጥ የሰበሰቡት ሀብትና ገንዘብ ቤት ንብረት ከየት መጣ ያሰኛል ; ሰው ሀብትና ንብረቱ እየበዛ ሲመጣ ደህንነት እየተሰማው ስለማይመጣ ያለውን ሀይል ሁሉ ተጠቅሞ እራሱን አስተማማኝ ደህንነት ውስጥ ለማስቀመጥ ይተጋል፡፡ዛሬ በሰላማዊና በዲሞክሪያሲያዊ ትግል ውስጥ ሰላማዊና ዲሞክሪያሲያዊ ትግል እንዳይኖር ባለ ስልጣንን መሰረት አድርገው ሀብታሞች የሆኑና በስልጣናቸው ተጠቅመው ሀብትን የሰበሰቡ ሰዎች አንዱ መሳሪያ ናቸው፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት እንዲማቅቅ የሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ስልጣን ትክክለኛ ዓላማው ላይ ስላላዋልነው ነው፡፡ዛሬ በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ሆነ ዛሬ ወደ ስልጣን ሊመጡ የሚፈልጉት ፓርቲዎች በምን ዓላማ ላይ ተሞልተው ነው፡፡ገዢው ፓርቲ በስልጣን ላይ መቆየት የሚፈልገው ለምንድነው ; ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ደህንነት ድህነትን ከሀገሪቱ ለማጥፋት ነውን ; ይሄ ቢሆን ኖሮ ለሕዝቡ ነጻነትን ይሰጥ ነበር ዱላና በትሩን የኑሮ ጥያቄና የሰላም ጥያቄ በሚጠይቁ ድሆች ላይ አያሳርፈውም ነበር፡፡ዛሬ ባለው ላይ ለመጨመርና ያለውን አስተማማኝ ለማድረግ ነው ስልጣኑን ለማቆየት የሚታገለው፡፡ዛሬ ሕዝብ እንዲወክላቸው የሚፈልጉና ዛሬ ለምርጫ ደፋ ቀና የሚሉት ቢመረጡና ወደ ስልጣኑ ቢመጡ በእውነት ይሄ የመረጣቸውን ህዝብ ያከብሩት ይሆን ለዚህስ ለድሃው ሕዝብ ፍላጎት ይኖሩ ይሆን ; ዛሬ ብዙዎች አለአግባብ የሰበሰቡት ሀብት ለመሆኑ የማን ነው ; የሀገሪቱ ሀብት አይደለምን ሠርተውና ለፍተው ካገኙት በስተቀር አብዛኛው ዛሬ እታች አይታችሁት ነገ በድንገት እላይ ወጥቶ የምታዩት ሀብት ሁሉ ንፁህ ሀብት አይደለም፡፡ዛሬ መዝገቡ ቢመረመርና ምንጩ ቢፈተሽ ስንቱ ሊያዝ እንደሚችል እራሳቸው በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጣሉ የሚያጋልጡአቸውን በስልጣናቸው ላይ የባለጉትን ባለስልጣናትና ከባለስልጣናት ጋር አብረው የተጋለጡትን ሀብታሞች ማየት እንችላለን፡፡ለምሳሌ እነ ታምራት ላይኔና መሰል ባለስልጣኖቻቸው ሲጋለጡ አብረው የተጋለጡ ባለሀብቶች እንደነበሩ የኢትዮጵያ ዜና ማሰራጫ እራሱ ይመሰክራል፡፡በቅርቡም የጉምሩክ ባለስልጣናት ስልጣናቸውን መሰረት አድርገው የሰበሰቡት ገንዘብ ለሕዝብ ሲታይ በከተማችን የሚታወቁ አስመጪና ላኪ ሀብታሞች ስማቸው መጠራቱን አሁንም የኢትዮጵያ ቴሊቭዥን ይመሰክራል፡፡ስለዚህ እነዚያና እነዚህ የተያዙት ባለስልጣናት በገንዘብ ወፍረው ከጀርባቸው ባለሀብቶችን መሠረት አድርገው ካሉ ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉትስ ስንቶቹ ከዚህ ችግር የፀዱ ናቸው ለማለት ያስችላል፡፡ስለዚህ ነው እንግዲህ በባለሀብቱ ስም በሙሰኝነት የወፈሩና የጠገቡ ባለስልጣናት የድሃውን የኢትዮጵያ ህዝብ መሬትና ጉልበት የሚበዘብዙ ፤ለምን ሲል በፌዴራል ፖሊስ ዱላ ዝም ለማሰኘት የሚጥሩ ገንዘብና ስልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ አይደለምን ; በአጭር ጊዜ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ ድሆች ሊደርሱበት እስከማይችሉ የተማሩ ሰዎች ትምህርት ለምኔ እስከሚሉ የደረሱበት ጊዜ መሆኑን ባለስልጣናቱ ልብ ያሉት አይመስሉም፡፡ይልቁንም በዚያው ፍጥነት ለመሮጥና ቦታ መሬት ቤቶች በስማቸውና በዘመዶቻቸው ስም ንብረት ለማከማቸት እየሮጡ መሆኑን ስንመለከት በሀገራቸው አልበቃ ብሎአቸው ከሀገር ውጪም ቤት ለመግዛት ሀብት ለመሰብሰብ ሲጥሩ ስልጣን ገንዘብንና ሀብትን ለመሰብሰብ ምን ያህል እንደጠቀማቸው ያሳያል፡፡
ዛሬ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉትም ልዩ ልዩ ፓርቲዎች በምን ዓላማ ላይ ተመስርተው ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ የድሃው ሕዝብ መንገላታት ተሰምቶአቸው ይሆን ; ይህ ከሆነ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ቀጥሎም ራዕያቸውና ሕልማቸው ተመዝኖ ልንመርጣቸው ይገባናል፡፡ገዢው ፓርቲም ለምን ምረጡኝ እንዳለ ጭቁኑን ስደተኛውን በእነዚህ 20 አመታት ውስጥ ለስደት የተዳረገውን ኢትዮጵያዊ በፌዴራል ፖሊስ እየተደበደበ እንኳ ኩሪፊያውንና አልገዛም ባይነቱን ሲመለከት ምን ይማራል ; ሀይልና ስልጣንን ተጠቅሞ በግድ መግዛት እስከመቼ ያስኬድ ይሆን ; የት ድረስ ይቀጥል ይሆን ብላችሁ ልትጠይቁ ይገባል፡፡ገዢው ፓርቲ በስሩ ያሉትን ባለስልጣናትንና በኢትዮጵያ ህዝብ አላግባብ የወፈሩትን ሀብታሞች ሁሉ ሰብስቦ ከፍተኛ ምክክር ሊያደርግና በኢትዮጵያ ውስጥ የከበደውን ውጥረት ሊያረግብ ሲልም ችግሮችን ሊፈታ የሚችልበትን መንገድ መከተል ይኖርበታል፡፡ይሄም አንደኛው የኢትዮጵያን ህዝብ ዲሞክሪያሲያዊ መብት ማስከበር የመረጠውን ማስተናገድ የሀብት ክፍፍሉን ለሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እንደ አስፈላጊነቱ እኩል ማካፈልና ያላግባብ የወፈሩ ባለስልጣናትንና በግፍና ያለ ሕግ ሀብት የሰበሰቡትን ባለሃብቶች ማጋለጥና ሕገ መንግስቱ በሰጠው መብት መሠረት ፍርድ ቤቶች ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል መስራት እንዲችልና ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግና ይሄንን በእርምጃው ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡አለበለዚያ ሀገሪቱ ፊት ለፊት ከፍተኛ አደጋ ሊገጥማት እንደሚችል ያለ ጥርጥር መናገር ያስችላል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment